የአረንጓዴ ኢኮኖሚን በመገንባት የብልጽግና ትልሞችን ዕውን የማደረጉ ጉዞ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር)

ሚኒስትሩ ድሬዳዋ የሚገኘውን ሬድዋ ሞተርስ የመኪና ማምረቻ ፋብሪካን የስራ እንቅስቃሴን ጎብኝተዋል።

ከጉብኝቱ በኋላ ባስተላለፉት መልዕክት የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታን በማጠናከር የብልጽግና ትልሞችን ዕውን የማድረጉ ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አንስተው ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በሬዳዋ ሞተርስ የመኪና ማምረቻ እየተመረቱ የሚገኙ በታዳሽ ኃይል የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች የዚሁ ጉዞ ጥሩ ማሳያ መሆናቸውን በመጠቆም።

እየተመረቱ የሚገኙት ተሽከርካሪዎች የውጭ ምንዛሬ ወጪን ከማዳን ባለፈ የተሽከርካሪ ዕጥረትን በመፍታት ለትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፍ ዕድገት አይነተኛ ሚና ያበረክታሉ ብለዋል።

በኢትዮጵያ ታምርት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ንቅናቄ ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረትና የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘት የተጀመረውን ጉዞ ለማሳደግ የላቀ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑንም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ባለፉት ሰባት የለውጥ ዓመታት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ በመገንባት በኩል እመርታዊ ለውጥ ማምጣት መቻሉን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ፣ የብዝሃ ዘርፍ የኢኮኖሚ ዕድገት ግስጋሴ፣ የጉባ ብስራቶችን ጨምሮ ሌሎችም የኢትዮጵያን እድገትና ማንሰራራት የሚያስቀጥሉ መሆናቸውን አንስተዋል።

የሬዳዋ ሞተርስ ኢንዱስትሪ የማምረቻ ክፍል ስራ አስኪያጅ ኢሳያስ አክሊሉ በበኩላቸው የድሬዳዋ አስተዳደርም ሆነ የፌደራል መንግስት ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ እያደረጉት ላለው ድጋፍና ክትትል አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

የተደረገው ጉብኝትና የተሰጣቸው ምክረ ሃሳብ የበለጠ በትጋት ለመስራት የሚያበረታቸው መሆኑን ጠቅሰው ተሽከርካሪዎቹን ለገበያ ለማቅረብ ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል።

በ100 ሄክታር መሬት ላይ የተገነባው ሬድዋ ሞተርስ ኢንዱስትሪ በኤሌክትሪክና በነዳጅ የሚሰሩ የጭነትና የሰው ማመላለሻ ተሽከርካሪዎችን እያመረተ ይገኛል።

Share this Post