በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) አዘጋጅነት በብሉ ኢኮኖሚ ላይ ያተኮረ አውደጥናት ተከፈተ
መድረኩ የተዘጋጀው የብሉ ኢኮኖሚ ተቋማትን በአንድ መድረክ ለማገናኘት እና የብሉ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ አፈጻጸም እቅድ ላይ ለመወያየት ነው።
የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዴንጌ ቦሩ በመክፈቻ ንግግራቸው አገሪቷ በሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች ያሳየችውን እምርታ የገለጹ ሲሆን ለብሉ ኢኮኖሚ ያላትን ቁርጠኝነት አፅንዖት ሰጥተው ብሄራዊ ቅንጅታዊ አሰራርን ለማጠናከር በቅርቡ የተደረጉ ጥረቶች ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ በኢጋድ ብሉ ኢኮኖሚ ማዕቀፍ ውስጥ ሀገሪቱን እንዲወክል የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴርን መወከሏን ጠቅሰው ይህም መንግስት የተቀናጀ ቀጠናዊ ትብብር ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነት አመላካች በመሆኑ ሚኒስቴር መስሪያቤቱ የተሰጠውን ሀላፊነት በትጋት እየተወጣ ነው ብለዋል።
እንደሀገር ብሉ ኢኮኖሚን ከብሄራዊ ልማት እቅድ ማዕቀፉ ጋር ለማዋሃድ አስቻይ መንገዶችን መፈተሽ እና መተግበርም ለውሃና የውሃ ተያያዥ ሀብቶችን በዘላቂነት ለመምራት አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ የብሉ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ከየተቋሞቻቸው ሥራ ጋር ማቀናጀት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተሳታፊዎች በንቃት እንዲወያዩም ሚኒስትር ዴኤታው አሳሰበዋል።
አውደ ጥናቱ እድገትን ለመገምገም፣ ምርጥ ተሞክሮዎችን ለመለዋወጥ እና አገራዊ ውጥኖችን ከክልላዊ ስልቶች ጋር በማጣጣም ለዘላቂ ልማት፣ የባህር አስተዳደር እና ኢኮኖሚያዊ አቅም ለማቀናጀት መድረክ ሆኖ ያገለግላል።
በአውደጥናቱ እየተሳተፋ የሚገኙት የኢጋድ አባል ሀገራት ተወካዮች፣ የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ፣ ዩኒቨርስቲዎች እና ሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማት ቴክኒካል ባለሙያዎች ሲሆኑ ሁሉም በአፍሪካ ቀንድ ያለውን የብሉ ኢኮኖሚ አቅም ለመጠቀም በጋራ የሚሰሩ ናቸው።