"ስንተባበር ማሳካት እንደምንችል አገራዊ የአረንጓዴ ኣሻራ ኢንሼቲቭ ትልቅ ማሳያ ነው" ክቡር ዶ/ር አለሙ ስሜ
ጥናቱ የተካሄደው በኢትዮጵያ፣በ ICAO ፕሮግራም እና በአውሮፓ ህብረት የገንዘብ ድጋፍ ሲሆን ዘላቂ የአቪዬሽን ነዳጅ (SAF) ማልማት በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ የተደረገው የአዋጭነት ጥናት ግኝት እና የቢዚነስ ትግበራ ዕቅድ ለባለድርሻ አካላት ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ይገኛል።
በመድረኩ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር አለሙ ስሜ ስንተባበር ማሳካት እንደምንችል አገራዊ የአረንጓዴ ኣሻራ ኢንሼቲቭ ትልቅ ማሳያ ነው ብለዋል።
ክቡር ዶ/ር አለሙ አክለውም ቀጣይነት ወዳለው አቭዬሽን የሚደረገው ጉዞ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት በቁርጠኝነት ከምትሰራቸው ተግባራት አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።
የአረንጓዴ አሻራ ስኬትን መሠረት በማድረግ ስትራቴጂክ ዕቅድ በማዘጋጀት እና በጋራ ቅንጅት ከትራንስፖርት ዘርፍ የሚለቀቀውን የካርበን ልቀት ለመቀንስ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ተነሳሽነት በሁሉም ዘርፍ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትሉ በካይ ጋዞችን ለመቀነስ ያላትን ቁርጠኝነት ከማመላከቱም ባሻገር በተካሄደው የአዋጭነት ጥናት ውጤት መሰረት 80 በመቶ የአቭዬሽን ካርበን ልቀት ለመቀነስ የሚያስችል ስለመሆኑ ተመላክቷል።
በመድረኩ ላይ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር አለሙ ስሜ፣ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ደንጌ ቦሩ፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ አበራ፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የአለም አቀፍ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ተወካዮች እና ሌሎች የባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።