የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት የአሰራር ስርዓቱን ለማዘመን ተኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑ ተገለፀ
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ፣ መሰረተ ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት የአሰራር ስርዓቱን ለማዘመን ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሆነ ገለጸ።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ፕሮፌሰር መሐመድ አብዱ የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት በሰው ህይወት እና ንብረት ላይ የሚደርሰውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሆነ በሪፖርት የገለጸውን በተግባር በመስክ ምልከታ ለማረጋገጥ ነው ሲሉ የጉብኝቱን ዓላማ አስገንዝበዋል።
የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መሐመድ አሰን መንገድ የሚጠቀም ማንኛውም አካል ለአደጋ የተጋለጠ መሆኑን አስተውሰው፤ ይህንን አስከፊ አደጋ ለመቀነስ ለአሽከርካሪዎች እና ለማህበረሰቡ የግንዛቤ ማሰጨበጫ እየተሰጠ ነው ብለዋል።
ለአሽከርካሪዎች እና ለማህበረሰቡ በተፈጠረው ግንዛቤ አሁን ላይ የትራፊክ አደጋ እየቀነሰ መምጣቱን ገልጸዋል።
በህገወጥነት በተመሳሳይ ታርጋ የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎችን በመለየት በአዲሱ የተሽከርካሪ ሰሌዳ ወደ አንድ መስመር ለማምጣት በትኩረት እየተሰራ እንደሆነም አቶ መሐመድ አብራርተዋል።
የተቋሙን የአሰራር ስርዓት በቴክኖሎጂ በማዘመን ረገድ የሚከሰቱ የትራፊክ አደጋዎችን የተሟላ መረጃ ለመያዝ የሚያስችል ሲስተም የለማ መሆኑን አቶ ሚኪያስ መላኩ ለቋሚ ኮሚቴው አብራርተዋል።
ከሶስተኛ ወገን ኢንሹራንስ አገልግሎት ጋር በተገናኘ ስራዎችን ለማቀላጠፍ የ7660 የጥሪ ማዕከል ተደራሽ መሆን እንደቻለም መገለጹን የምክር ቤቱ መረጃ አመላክቷል ።