የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋማት የ6ወራት እቅድ አፈፃፀም አበረታች መሆኑ ተገለፀ።

በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን በኩል ባለፉት ስድስት ወራት የዓለም አቀፍ በረራዎች አገልግሎት የማሳለጥና የመደገፍ ስራዎች፤ የአየር ትራንስፖርት መሠረት ልማት የማስፋፋት እና የኤርናቪጌሽን አገልግሎት የማሳደግ፤ የነባር እና አነስተኛ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ፍቃድ የመስጠት፤ የአየር ደህንነት የማረጋገጥ ስራዎች መሰራታቸው በጥንካሬ ተገምግሟል፡፡

በመንገድ ደህንነት እና መድህን ፈንድ አገልግሎት በኩል የመንገድ ትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች፤ የተለያዩ አካላትን በመንገድ ደህንነት ዙሪያ የማሰልጠን እንዲሁም በርካታ የመንገድ የቁጥጥር ስራዎችን መሰራታቸውን በሪፖርቱ ተመላክቷል።

በፐብሊክ ትራንስፖርት አገልግሎት በኩል ለመንግሥት ስራተኞች የትራንስፖርት አገልግሎት የመስጠት፤የከተማ ትራንስፖርት አገልግሎት የመስጠት፤ ሀገር አቋራጭ የልዩ ትራንስፖርት አገልግሎት፤ ሰሌዳ የማምረት እና የማሰራጨት እና የአሽከርካሪዎች ስልጠና በዋናነት እንደተተገበሩ ተገልጿል ።

በኢትዮዽያ ማሪታይም ባለስልጣን የሞጆ ሎጂስቲክስ ማዕከል ግንባታ ማጠቃለያ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ የተገመገመ ሲሆን አጠቃላይ በተሽከርካሪ በባቡር እና በአየር ትራንስፖርት የተጓጓዙ ገቢ እና የወጪ ጭነቶች እያደገ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት በኢትዮዽያ ምድር ባቡር በኩል ሀገሪቱን የወጪ እና የገቢ ዕቃዎች፤ የባቡር መንገደኞች አገልግሎት ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ የጨመረ ሲሆን አፈጻፀሙም ከፍተኛ ለውጥ የታየበት መሆኑ ተገምግሟል፡፡

በመጨረሻም የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ ክቡር ዶ/ር አለሙ ስሜ የዘርፉ የ6ወራት አማካይ የስራ አፈጻጸም ከ94% በላይ መሆኑ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው ብለዋል።

ክቡር ሚኒስትሩ ከሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት ጋር ተያይዞ ዘርፋ የተሰጠውን ተልዕኮ እየተወጣ ነው ያሉ ሲሆን ቀሪ ስራዎችን በተመለከተ ለሁሉም ተጠሪ ተቋማት የስራ ኃላፊዎች የስራ አቅጣጫ ሰጥተዋል።

Share this Post