ቦይንግ የአፍሪካ ቢሮውን በአዲስ አበባ ከፈተ

ክቡር ሚኒስትሩ የቦይንግ ኩባንያ የአዲስ አበባ ቢሮውን በከፈተበት ስነስርዓት ላይ ተገኝተው የቢሮው መከፈት በዓለም አቀፉ አቪዬሽን የኢትዮጵያን እድገት ማሳያ ከመሆን ባሻገር የተሳሰረችና የበለፀገች አፍሪካን እውን የማድረግ አለም አቀፋዊ ራዕያችንን ለማሳካት የሚያግዝ እርምጃ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ እያደገ የመጣ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ አቅም መፍጠሯን የጠቆሙት ክቡር ሚኒስትሩ በብሔራዊ ትራንስፖርት ካውንስል የሚመራ የዘርፉን መሠረተ-ልማት ለማዘመን፣ የትራንስፖርት ንግድ ወጪን ለመቀነስ እና አፍሪካን ለማስተሳሰር የሚያስችል የአስርት አመታት ፍኖተ ካርታ አዘጋጅተን እየሰራን ነው ብለዋል፡፡

በዘርፉ የ10 አመት የልማት እቅድ ላይም በባቡር፣ በወደብ ልማት፣ በአቪዬሽን እና በስማርት ሎጂስቲክስ ዘርፍ እንደ ቦይንግ ካሉ የግል ሴክተሮች ጋር በጋራ የምንሰራበት የ74 ቢሊየን ዶላር የኢንቨስትመንት እቅድ መቀመጡንም ጨምረው አንስተዋል፡፡

የቦይንግ ኩባኒያ አመራር በኢትዮጵያ ላይ ባሳደረው እምነት አመስግነው ይህንን አጋርነት የአውፕላን ክፍሎችን በማምረት፣ ስልጠናዎችን በመስጠትና በዘላቂ የአቪዬሽን ነዳጅ ላይ በትብብር በመስራት አጋርነታችንን እናሳድግ ብለዋል፡፡

በጋራ ሆነን የኢትዮጵያ አየር መንገድን ወደ አለምአቀፍ የአቅርቦት ሰንሰለት መሪነት ከፍ ማድረግ እና አዲስ አበባን የአፍሪካ የኤሮስፔስ ፈጠራ ማዕከል ማድረግ እንችላለን ሲሉ አክለዋል፡፡

የቦይንግን የአፍሪካ ቢሮ በአዲስ አበባ ስንከፍት የኢትዮጵያ ሰማይ ድንበር ሳይሆን መግቢያ በር መሆኑን ማስታወስ ይኖርብናል ያሉት ክቡር ሚኒስትር ዶ/ር ዓለሙ ስሜ፤ መግቢያ በርነቱም ለኢኮኖሚ ነፃነት፣ ለአህጉራዊ አንድነት፣ ለዓለማቀፋዊ አቪዬሽን እድገት አፍሪካ ድርሻዋን እንድትወጣ በማድረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ቦይንግ ቢሮውን በአዲስ አበባ በከፈተበት ሥነ-ስርዓት ላይ የቦይንግ የመካከለኛው ምስራቅ፣ ቱርክ፣ አፍሪካ እና ማዕከላዊ ኤዥያ ፕሬዝዳንት ሚስተር ኩልጅት ጋታ፣ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ፣ የኢትጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግስቴ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰውና ሌሎችም የኩባንያው አመራሮች ተገኝተዋል፡፡

Share this Post