የግል አየር ትራንስፖርት ኦፕሬተሮች በስፋት እንዲገቡ መንግሰት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተገለፀ፡፡
ከግል አየር ትራንስፖርት ኦፕሬተሮች ጋር በዘርፋ የሚያጋጥሙ ችግሮችን አስመልክቶ ከክቡር ዶ/ር አለሙ ስሜ እና የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮሀንስ አበራ ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡
ከተሞችን እርስ በእርስ የማስተሳሰር የበረራ አገልግሎት መስጠት፣ ዓለም አቀፍ በረራዎችን ከአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት በተጨማሪም በሌሎች የሀገራችን ክልሎች ኤርፖርቶች ማስተናገድ፣ ዓለም አቀፍ በረራዎችን በአፍሪካ ውስጥ እና የዓለምአቀፍ መዳረሻዎች መካከል ማድረግን በተመለከተ ከግል ኦፕሬተሮች ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡
የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር አለሙ ስሜ የአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ከሀገሪቱ የግብርና፣ የኢንደስትሪ፣ የማዕድን፣ የቱሪዝም፣ እድገት ጋር ተያይዞ አብሮ እያደገ በመሆኑ የግል አየር ትራንስፖርት ኦፕሬተሮች በስፋት ተሳታፊ ቢሆኑ ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ተናግረዋል፡፡
ክቡር ሚኒስትሩ የህብረተሰቡ የአየር ትራንስፖርትን የመጠቀም ፍላጎቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ ዘርፋን በማዘመን እና በማስፋፋት በ2018 በጀት ዓመት የአየር ትራንሰፖርት አሁን ካለበት የተሻለ አገልግሎት መስጠት እንዳለበት ገልፀዋል፡፡
ትራንስፖርቱን ለማዘመን እና ለማስፋፋት ባለፉት ሰባት ዓመታት በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል፡፡
ክቡር ሚኒስትሩ አነስተኛ የአውሮፕላን ማረፊያዎች እና ኤር ስትሪፖች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከመንግስት ትልልቅ ፕሮጀክቶች፣ ከቱሪዝም መዳረሻዎች እና ከማዕድን ምርታማነት ጋር ተያይዞ እየተሰፋፋ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮሀንስ በበኩላቸው የሚሰጡ አገልግሎቶችን ለማዘመን አሰራሮችን ዲጂታላይዝ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆንን ገልጸው ለግል ኦፕሬተሮች አሁን የተሻለ ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ ነው ብለዋል፡፡