የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ለማስፋፋት የልምድና ተሞክሮ ልውውጥ ወርክሾፕ እየተካሄደ ይገኛል።

ኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ላይ ያላትን ፓሊሲ እና ስትራቴጂ እንዲሁም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪን ለማስፋፋት የተሰሩ ስራዎች ተሞክሮ በወርክሾፕ ቀርቧል።

በወርክሾፕ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ በርኦ ሀሰን በኢትዮጵያ ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ የሚደረገው ሽግግር ከትራንስፖርት እንቅስቃሴ በዘለለ ዘላቂ በሆነ መልኩ አካባቢን ለመጠበቅ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለማረጋገጥ እንደሚያስችል ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ በሀያ ሰላሳ 500 ሺህ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች እና 2,176 ቻርጅ ስቴሽን ለመስራት እቅድ ተይዞ እየተሰራ እንደሚገኝ ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ለማስፋፋት እያጋጠመ ያለውን የፋይናንስ፣ የመሰረተ ልማት፣ በዘርፉ የሰለጠነ ባለሙያዎች ለማፍራት ያሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት በዘርፋ ልምድ ያላቸው ሀገራት ድጋፍ አሰፈላጊ መሆኑን ሚኒስትር ደኤታው አክለው ገልጸዋል።

ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ለማስፋፋት ይህ ወርክሾፕ የተሻለ ልምድ እና እውቀት ለማግኝት እንደሚያግዝም አብራርተዋል።

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ ይዘንጋው ይታይህ በኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ አስመልክቶ የወጡ ፓሊሲና ስትራቴጂ፣ የህግ ማዕቀፎች፣ እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶች አንዲሁም የኤሌክትሪክ ለማስፋፋት የተሰሩ ስራዎችን አስመልክተው ለተሳታፊዎች አቅርበዋል።

ወርክሾፕ በእንግሊዝ መንግስት ድጋፍ የተዘጋጀ መሆኑን እና እንግሊዝ 26 ዓመታት ያላትን የኤሌክትሪክ ታክሲ ተሽከርካሪ፣ የኤሌክትሪክ ባቡር፣ ባትሪ ስቴሽን እና መሰረት ልማት ለማስፋፋት ልምድ ለማካፈል መሆኑን የወርክሾፕ አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ ሀይሉ ተናግረዋል።

ወርክሾፑ በዘርፋ የተሰማሩ ድርጅቶች ባሳተፈ መልኩ ለተከታታይ ሁለት ቀናት በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች የሚካሄድ ይሆናል።

Share this Post