ከእቅድ እና ከሃሳብ ባለፈ ወደ ተግባር የምንገባበት ጊዜ አሁን ነው"ክቡር አቶ ደንጌ ቦሩ
በኢትዮጵያ የሎጂስቲክስ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውና በዘርፉ ያለውን የክህሎት ክፍተት ለመሙላት ያለመው "የብቃት ማረጋገጫ ማዕቀፍ እና የሥልጠና ፍላጎት ጥናት" የማረጋገጫ መድረክ (Validation Workshop) ተካሂዷል ።
የአውደ ጥናቱ ዓላማዎች እና ግኝቶች፣
በመድረኩ ላይ በጥናቱ የተለዩ የክህሎት ክፍተቶች፣ የተዘጋጀው የብቃት ማዕቀፍ (Competency Framework) እና ለሁሉም የሙያ ደረጃዎች የቀረበው የሥርዓተ-ትምህርት መዋቅር (Curriculum Structure) በባለድርሻ አካላት ተገምግሞ ጸድቋል።
ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ሀገር እንደመሆኗ፣ ቀልጣፋ የሎጂስቲክስ ሥርዓት ለኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት መሆኑ በጥናቱ ተመላክቷል።
ጥናቱ ዘርፉን በብቁ ባለሙያዎች በመምራት የትራንስፖርት ወጪን ለመቀነስ እና የንግድ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ ያለመ መሆኑም ተጠቁሟል ።
ጥናቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ (AAU) አማካኝነት፣ የዘርፉን ባለሙያዎች (Practitioners) በማሳተፍ ተከናውኗል።
ከዚህ በፊት በተበታተነ መልኩ ከሚሰጡ ስልጠናዎች በተለየ፣ ይህ ፕሮግራም ለመጀመሪያ ጊዜ የአስፈጻሚ አካላትንና የንግድ ድርጅቶችን ፍላጎቶችን ያማከለ፣ ሳይንሳዊ እና አጠቃላይ የብቃት ማረጋገጫ ሥርዓት መሆኑም ተገልጿል ።
በቀጣዮቹ ሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ፕሮጀክቱ ወደ pilot ትግበራ የሚገባ ሲሆን፣ በአዲሱ የብቃት ማዕቀፍ መሰረት ስልጠናዎች እንደሚሰጡም ተጠቁሟል።
የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ደንጌ በዚህ ጊዜ ባስተላለፋት መልዕክት ከእቅድ እና ከሃሳብ ባለፈ ወደ ተግባር የምንገባበት ጊዜ አሁን ነው ብለው ዘርፉን ለማዘመን ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።